avatar
Meseret Media
@meseretmedia
16.03.2026 22:03
#ዜናመሠረት "ሰሞኑን የታየው የነዳጅ ስርጭት መዛባት እና እጥረት ችግር የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትሩን እንዲሁም የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩን ጭምር የሚመለከት ነው"- የመንግስት የመረጃ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ

(በበርካታ የመሠረት ሚድያ ተከታታዮች ጥያቄ በድጋሜ ለሁሉም ክፍት ሆኖ የቀረበ)

(መሠረት ሚድያ)- ሰሞኑን በስፋት ከታየው የነዳጅ ግዥ፣ የስርጭት እጥረት እና መዛባት ጋራ በተገናኘ የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን ሦስት ከፍተኛ ሓላፊዎች እንዲሁም 18 የሚደርሱ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ንግድ ጽሕፈት ቤት አመራሮች በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ሐላፊዎቹ የባንክ ሒሳባቸው ታግዶ ምርመራ እየተጠራባቸው ይገኛል፣ ሆኖም የእስር እርምጃው የችግሩ ዋና ምንጮች ያልተለዩበትና ዘላቂ መፍትሔ የማያመጣ እንደኾነ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

በችግሩ የተጠረጠሩት የባለሥልጣኑ የነዳጅ ዘርፍ ምክትል ዋና ዲሬክተር አቶ ዲበራ ፉፋ፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስመለዓለም ምሕረቱ እና ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ባለፈው ሰኞ የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

በዕለቱ ከቀኑ 11፡00 ገደማ በሥራ ላይ እያሉ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሁለቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ተይዘው ከመወሰዳቸው አስቀድሞ እስከ ምሽቱ 2፡00 ድረስ ቢሯቸው ፍተሻ እንደተደረገበት የመሥሪያ ቤቱ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ ገልጸዋል፡፡

ሰሞኑን የታየው የነዳጅ ስርጭት መዛባት እና እጥረት ችግር “የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትሩን እንዲሁም የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩን ጭምር የሚመለከት ነው” የሚሉት ምንጮቹ በእነርሱ ትእዛዝ ጉዳይ የሚፈጽሙ ሓላፊዎችን ብቻ ተጠርጣሪ ማድረግ ፍትሐዊ መስሎ እንደማይታያቸው አመልክተዋል፡፡ 

ሕገወጥ የነዳጅ ስርጭትን ለመቆጣጠርና በማደያዎች መካከል የሚታየውን አድሏዊ የጭነት አሠራር ለመቅረፍ፣ በባለሥልጣኑ የወጣውን የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች የገበያ ድርሻ ድልድል ያስታወሱት ምንጮቹ በተለይ ሚኒስትሩ አቶ ካሳሁን ጎፌ ክፍፍሉን በቀመሩ መሠረት ከማስፈጸም ይልቅ የግል ጥቅማቸው ማስጠበቂያ ማድረጋቸው የችግሩ ዋና መንሥኤ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች የሎጅስቲክስ ዐቅም እና ልምድ የነዳጅ ገበያ ድርሻቸውን እንደሚወስን የጠቀሱት ምንጮቹ በሚኒስትሩ አቶ ካሳሁን ተሰጠ ባሉት ቀጥተኛ ሕገወጥ ትእዛዝ በጊዜ ሒደት ከፍተኛ ዐቅም የፈጠሩ ኩባንያዎች ድርሻ ተነጥቆ በቂ ልምድ እና የሎጂስቲክስ ዐቅም ለሌለው አንድ ኩባንያ መሰጠቱ የሰሞኑን የነዳጅ ስርጭት መዛባት ከፈጠሩት ምክንያቶች አንዱ እንደኾነ ገልጸዋል።

በነዳጅ ገበያ ድርሻ ክፍፍል ሊጠቅሙት ያሰቡትን ኩባንያ ድርሻ በማሳደግ፣ ቀደም ሲል ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን ኩባንያዎች ከገበያ ማስወጣት ዋና ዓላማቸው እንደኾነ ሚኒስትሩ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ በከፍተኛ ሓላፊዎች ስብሰባ ላይ በግልጽ ያነሡ እንደነበር ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ነበርን ያሉ ምንጮች አውስተዋል፡፡

የነዳጅ ስርጭትን ለማሳለጥም ኾነ ለማዛባት ከፍተኛ ሚና ያላቸው አከፋፋይ ኩባንያዎች በዚኽ መሰሉ የጥቅም ሰንሰለት በመማረር ከሚኒስትሩ ጋራ ግልጽ ፍጥጫ ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ ባለፈው ሳምንት ዐርብ በተካሔደ የሴክተሩ ስብሰባ ላይ መስተዋሉን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪ ሚኒስትር በኾኑት ግርማ ብሩ በተመራው በዚያ ስብሰባ በሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ እና በኩባንያዎቹ መካከል የተካሔደው ክርክር “ስድብ ቀረሽ እና እልክ አስጨራሽ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡

በመጨረሻም በአማካሪ ሚኒስትሩ ግርማ ብሩ የተሰጠው አቅጣጫ የነዳጅ ስርጭቱ ችግር ዋና ባለቤት እና ምንጭ “የባለሥልጣኑ አመራሮች በተለይም ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ እንደኾኑ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው” ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

የሰሞኑ የነዳጅ ስርጭት እጥረት እና መዛባት መሠረታዊ ችግር የአመራር፣ የመዋቅር እና የአሠራር ውስንነት፣ በተለይም አኹን በሓላፊነት ላይ ያሉ አመራሮች ችግር እንደኾነ እንደ አቶ ግርማ ብሩ ባሉ ባለሥልጣናት ዘንድ ከበቂ በላይ ከታወቀ ዘንድ በሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ላይ ርምጃ አለመወሰዱ ግራ እንዳጋባቸው የመሥሪያ ቤቱ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሰኞ በባለሥልጣኑ የነዳጅ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዲባራ ፉፋ እና በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ላይ ያተኮረውን የእስር ርምጃም “አህያውን ትቶ ዳውላውን” ሲሉ ተችተዋል፡፡ 

የቀድሞዎቹን ሓላፊዎች ከቦታቸው በማንሣት አሁን ያሉትን ዋና ዳይሬክተሩንና ለእስር የተዳረጉትን ሦስቱን ሓላፊዎች ወደ ሥልጣን አምጥተው ያሾሟቸው ሚኒስትሩ ካሳሁን እንደሆኑ ያወሱት ምንጮቹ ወደ ቢሯቸው በተደጋጋሚ እየጠሩ በማስፈራራት ጭምር የጥቅም ሰንሰለታቸው አስፈጻሚ እና ተላላኪ አድርገዋቸው እንደቆዩ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

“በሙስናው ረገድ ቢሳካላቸውም በአመራር ድክመት እና ዐቅመ ቢስነት ምክንያት ግን ችግሩ እየፈጠጠ መጣና በቅርቡ መነጋገሪያ መኾን ቻለ፡፡ በዚኽም ምክንያት የተወሰኑ አመራሮች ለእስር ተዳረጉ፤ እነዚኽን ሰዎች እንደ ጦስ ዶሮ በመጠቀም አሁንም ተቋማዊ ሪፎርም እያደረግን ነው፤ በሚል ፌዝ መንግሥትንና ሕዝብን በማታለል ላይ ይገኛሉ” ይላሉ፡፡

ሦስቱ ታሳሪዎች ያለቦርዱ ውሳኔ የሚኒስትሩን ሕገ ወጥ ትእዛዝ በመፈጸም በድርሻቸው ሊያስጠይቃቸው የሚችል ጥፋት ሊኖር እንደሚችል ያልሸሸጉት ምንጮቹ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በርግጥ ታስቦ ከኾነ ግን “የችግሩ ምንጭ የኾኑትን አመራሮች በሙሉ ከሓላፊነት ማንሣትና በሕግም እንዲጠየቁ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ አመልክተዋል፡፡

በዚህ ዙርያ የሚኒስትር ካሳሁን ጎፌን አስተያየት ለማካተት ያረግነው ሙከራ አልተሳካም።

-መሠረት ሚድያ-

@MeseretMedia
195
👍 50
😱 14
🤔 11
👏 8
😁 2
🎉 2
🕊 2
86 30.8K

Обсуждение 0

Обсуждение не доступно в веб-версии. Чтобы написать комментарий, перейдите в приложение Telegram.

Обсудить в Telegram

Meseret Media

68.4K
Facts matter!
www.meseretmedia.org
Открыть в Telegram