#EthiopiaCheck 'መረጃን ከማጋራትዎ በፊት ያስተዉሉ'- ዛሬ እየተከበረ ከሚገኘዉ ዓለም አቀፍ መረጃ ማጣራት ቀን ጀርባ ያለ መልዕክት
/ኢትዮጵያ ቼክ/- በዛሬዉ እለት ዓለም አቀፍ የመረጃ ማጣራት ቀን (International Fact-Checking Day) በመላዉ አለም እየተከበረ ይገኛል።
ይህ በየዓመቱ እኤአ ሚያዚያ 2 (April 2) የሚከበረዉ ቀን መረጃ አጣሪዎች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በመዋጋት ረገድ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ታስቦ ከ10 ዓመታት በፊት እኤአ በ2016 በየአመቱ እንዲከበር በተወሰነው መሰረት ነበር።
ከዛ ወዲህም በየአመቱ የመረጃ ማጣራትን አስፈላጊነት ግንዛቤን የሚያሳድጉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሲከበር ቆይቷል።
ይህ ቀን በሀገራችን ከፍተኛ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በሚታይበት በተለይ ሰው-ሰራሽ አስተውሎት የሚፈበረኩ ይዘቶች በርካቶችን ለተሳሳተ ግንዛቤ ሲዳርጉ በሚታይበት ወቅትም እየተከበረ ይገኛል።
ስለዚህም ቀኑ መረጃ ማጣራት ክህሎት ለሀገራችን ዜጎች ከመችዉም ጊዜ በላይ አስፈላጊ በሆነበት ወቅት እየተከበረ እንደሚገኝ ልብ ልንለው ይገባል።
በሀገራችን ዉስን መረጃ አጣሪዎች ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎችን በማጋለጥ ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃን እንዲያገኝ ዉስን እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ይሁን እንጂ ሀሰተኛ መረጃን መዋጋት እና ስርጭቱን መግታት ለመረጃ አጣሪዎች ብቻ የሚተዉ ተግባር አይደለም። ሁላችንም ሀሰተኛ መረጃዎችን ከማጋራት በመቆጠብ እንዲሁም የተሰራጩትን በማጋለጥ ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።
በተጨማሪም የሚዲያ አጠቃቀም ክህሎትን በማዳበር ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ያለንን ተጋላጭነት መቀነስም ያስፈልጋል።
ይህ ከሆነ የመረጃ ምህዳሩ ጤነኛ እንዲሁም ትክክለኛ መረጃዎች ጎልተዉ የሚታዩበት ይሆናል። ንቁ እና ስለ ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ጉዳት እና መከላከያ መንገዶች ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ እንዲፈጠርም አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ስለዚህ ዛሬ እየተከበረ የሚገኘዉን ዓለም አቀፍ መረጃ ማጣራት ቀን በምናከብርበት ወቅት እነዚህን ነጥቦች ልብ እንበል፡
-ተአማኒ ባልሆኑ የመረጃ ምንጮች የሚጋሩ መረጃዎችን ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ቆም ብለን እናስብ
-የመረጃ ምንጩን ተአማኒነት እናረጋግጥ
-መረጃዉ በማስረጃ የተደገፈ መሆኑን እንመርምር
-መረጃዉ በሌሎች የመረጃ ምንጮች በተለይም ተአማኒ በሆኑ ምንጮች መሰራጨቱን እናረጋግጥ
-የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመግታት የራሳችንን አስተዋጽኦ እናድርግ
ኢትዮጵያ ቼክ!
@EthiopiaCheck
Обсуждение 6
Обсуждение не доступно в веб-версии. Чтобы написать комментарий, перейдите в приложение Telegram.
Обсудить в Telegram