በጋምቤላ ክልል በጸጥታ ስራ ከተመደቡ የሰራዊት አባላት ውጪ “የትኛውንም የጦር መሳሪያ” ይዞ የሚገኝ እና የሚንቀሳቀስ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የጸጥታ ኃይሎች “አስፈላጊው እርምጃ” እንደሚወሰዱ የክልሉ መንግስት አስጠንቀቀ።
ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል፤ የፌደራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት “ሰፊ ስራዎችን” እያከናወኑ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
የክልሉ መንግስት ይህን ያስታወቀው፤ ወቅታዊ የክልሉም ሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ምሽቱን ባወጣው መግለጫ ነው።
በጋምቤላ ከተማ እና በክልሉ ወረዳዎች ከሰሞኑ በተከሰተ “የጸጥታ ችግር” የሰው ህይወት መጥፋቱን እና ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግስት በዚሁ መግለጫው አንስቷል።
የጸጥታ ችግሩን “ትርምስ” ሲል የጠራው የክልሉ መንግስት መግለጫ፤ ለዚህ ተጠያቂ ያደረጋቸው “የክልሉ ህዝብ ሰላም መሆን እንቅልፍ የሚነሳቸው” እና “ግጭትና የሰው ሞት የሚያስደስታቸው” ያላቸውን “ኃይሎች” ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ እና ግጭት ይከሰት እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፤ “የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት ለማረጋገጥ” መንግስት “የአመራር ለውጥ” ማደረጉን ጠቅሷል።
አዲስ የመጡት አመራሮች የነበረውን “የጸጥታ ችግር በመፍታት”፤ በልማት እና በሰላም ግንባታ ስራዎች “በርካታ ውጤቶች” እንዲመዘገቡ “ጥረቶች እያደረጉ” እንደሚገኙ የክልሉ መንግስት ገልጿል።
የክልሉን ሰላም እና ልማት “ወደ ኋላ ለመመለስ የሚሰሩ” ሲል የክልሉ መንግስት የጠራቸው ኃይሎች፤ “በየቦታው ሰዎችን በመግደል” ወንጅሏቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
🔴ለዝርዝሩ ➡️
https://ethiopiainsider.com/2025/16813/
@EthiopiaInsiderNews
Обсуждение 0
Обсуждение не доступно в веб-версии. Чтобы написать комментарий, перейдите в приложение Telegram.
Обсудить в Telegram