በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተደጋግመው ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የባህር በር እና የቀይ ባህርን የተመለከቱ ጉዳዮች ይገኙበታል። የቀይ ባህር ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ የማቅረብ ዕድል ካገኙ 19 የፓርላማ አባላት መካከል በአራቱ ተነስቷል።
ጉዳዩን ከኤርትራ ጋር ባለው ግንኙነት ውስጥ እንዴት እንደሚታይ የጠየቁ ሁለት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባላት፤ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መድረክ ስለ ሀገሪቱ ሲነሳ ከሚነገርበት አካሄድ በተለየ መልኩ የኤርትራን ገዢው ፓርቲ “ሻዕቢያ” በሚል ስያሜ ሲጠሩት ተደምጠዋል። ከእነሱ አንዱ የሆኑት በተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ቋሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ቶፊቅ አብዱላሂ፤ ሻዕቢያ “ጸረ ሰላም ኃይል” ነው ብለዋል።
“የሻዕቢያ ቡድን የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ጥያቄ ለማዛባት፣ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ እና የሚያሰራጩ ኃይሎችን አሰማርቷል። በሀገራችን ውስጥ ግጭቶች እንዲባባሱ ተግቶ ከመስራት ጀምሮ የተለያዩ አፍራሽ ሙከራዎችን እያደረገ ይገኛል” ሲሉ ዶ/ር ቶፊቅ ወንጅለዋል።
የተቃዋሚው አብን የፓርላማ አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ዋና ትኩረቱን” እና “የፖለቲካ ጉልበቱን” አጣዳፊ የውስጥ ቀውሶችን ከመፍታት ይልቅ በውጭ ጉዳይ ላይ እንዲያርፉ ማድረጉ “‘የህዝብን ትኩረት ለመቀየር የተደረገ ጥረት ነው’ የሚል አስተያየት እንዲሰጥ አድርጓል” ብለዋል።
“በሀገሪቱ ውስጥ ካለው የውስጥ ችግሮች ክብደት አኳያ መንግስት ይህንን ከፍተኛ የፖለቲካ አቅም ለውጫዊ ግብ እና ዓላማ ከማዋል ይልቅ ተመሳሳይ ጉልበት እና ትኩረትን የውስጥ የፖለቲካ ግጭቶችን ለመፍታት እና ከራሱ ዜጎች ጋር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ለምን አይጠቀምበትም?” ሲሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
@EthiopiaInsiderNews
Обсуждение 0
Обсуждение не доступно в веб-версии. Чтобы написать комментарий, перейдите в приложение Telegram.
Обсудить в Telegram