በኢትዮጵያ የሚሰሩ ባለሀብቶች በተግዳሮት ወቅት ከመንግስት እና ከህዝብ ጋር የሚቆሙ “ታማኞች” መሆን እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ። በደህናው ጊዜ “ሀብት የሚያካብቱ” ባለሃብቶች፤ በችግር ጊዜ “ወደ ዱባይ የሚሸሹ መሆን የለባቸውም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
አብይ ይህን ያሉት ትላንት ማክሰኞ መስከረም 27 ለታማኝ ግብር ከፋዮች ሽልማት በሰጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ 700 ግብር ከፋዮች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ፤ መንግስት ከታማኝ የግብር ከፋዮች ጋር “በጹሁፍ ያልሆነ ስምምነት” መፈጸም እንደሚፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል። ስምምነቱ ከያዛቸው 3 ነጥቦች መካከል የመጀመሪያው “ለማህበራዊ ዓላማ” መስራት የሚለውን እንደሆነም አስረድተዋል።
“የግሉ ሴክተር ከትርፍ በላይ ማህበራዊ ዓላማን ያነገበ ስራ የእያንዳንዱ ኩባንያ፣ የስራ ኃላፊዎች እና ባለቤቶች አንዱ ዋነኛ ተልዕኮ መሆን አለበት። ሰርቶ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ግብር የሚከፍል ሰው፤ ከትርፍ በላይ ለማህበራዊ ዓላማ ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አብይ በሁለተኛነት ያነሱት ነጥብ፤ ባለሃብቶች በችግር ጊዜ ከመንግስት ጋር አብረው መቆም ያለባቸው መሆኑን ነው። “በታማኝነት ልናገለግላችሁ ስለወሰንን በስኬትም፣ በተግዳሮትም ከመንግስት እና ከህዝብ ጋር የምትጋሩ ታማኞች መሆን አለባችሁ። በደህናው ዘመን የምትሰበስቡ እና ሀብት የምታካብቱ፤ በችግር ጊዜ ደግሞ ወደ ዱባይ የምትሸሹ መሆን የለባችሁም። በመከራውም ጊዜ፣ በስኬቱም ጊዜ በጋራ ጸንተን የምንቆም መሆን አለብን” ሲሉ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
🔴 ➡️
https://ethiopiainsider.com/2025/16306/
@EthiopiaInsiderNews
Обсуждение 0
Обсуждение не доступно в веб-версии. Чтобы написать комментарий, перейдите в приложение Telegram.
Обсудить в Telegram